የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የግብርና ታክስ አሰባሰብን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

መስከረም 18/2015 (ዋልታ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በንብረት ላይ የሚጣል ግብርና ታክስን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ባለው ውይይት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የግብርና ታክስ አሰባሰብን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

ክልሎች 70 በመቶ የሚሆነውን በጀት በመንግሥት ድጎማ እንደሚያገኙ የገለፁት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ሁሉም ክልሎች በተቻለ አቅም በኢኮኖሚ ራሳቸውን ለመቻልና ከመንግሥት የሚያገኙትን በጀት በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ የግብርና ታክስ አሰባሰባቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ተገቢውን የግብርና ታክስ ገቢ እያገኘ አይደለም ያሉት አፈጉባኤው በዚህም አሉታዊ ጎኖች በማስከተሉ በርካታ መሰረት ልማቶችን ለማስፋፋት እክል እንደፈጠረበት አብራርተዋል፡፡

ሀገሪቱን ከድህነት ሰንኮፍ ለማላቀቅና የጀመረችውን የእድገት ጎዳና ለማፋጠን የተለያዩ አገራት የግብርና ታክስ አሰባሰብ ተሞክሮዎችን መመልከትና ማጥናት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የግብር አከፋፈልና አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አፈጉባኤው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በግብር አከፋፈልና አሰባሰብ ላይ በሚታዩ ከፍተኛ ክፍተቶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW