ኢሰመኮ በጋምቤላ በንጹሃን ሰዎች ላይ ግድያ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ኃላፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠየቀ

መስከረም 18/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል በጋምቤላ ከተማ በንጹሃን ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ፣ አካል ጉዳት እና የንብረት ዘረፋ የፈጸሙ እና ይህንን ድርጊት ሲመሩና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ኃላፊዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል ሲል ጠየቀ፡፡

ኢሰመኮ በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ በሸኔ እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) መካከል የተደረገው ውጊያን ተከትሎ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች የተወሰዱ እርምጃዎች በተመለከተ ከሰኔ 20 እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በድርጊቱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂ ቡድን፣ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂ ቡድን፣ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይሎች፣ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች እንዲሁም ድርጊቱን ሲመሩ እና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ኃላፊዎችም ጭምር መሳተፋቸውን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት በኋላ እንዲሁም ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም በዋናነት በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች፣ በሸኔ ታጣቂዎች እና መሣሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሣሪያ አውጡ በሚል ምክንያት ሴቶችና የአዕምሮ ሕመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ንጹሃን ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መገደላቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ቢያንስ 25 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በበርካታ ሰዎች ላይ የመደብደብና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን ኮሚሽኑ አርጋግጧል፡፡

ኢሰመኮ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ተጎጂዎች ፍትሕ እና ተገቢውን የካሳ እና መልሶ መቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል እንዲረዳ ያከናወነው ምርመራ፣ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች በሪፖርቱ ያቀረበ ሲሆን ተፈጻሚነቱን የሚከታተል መሆኑንም አስታውቋል።