የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ጎበኙ

መስከረም 19/2015 (ዋልታ) የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መህሙድ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋናው መስሪያ ቤት በመገኘት የስራ ጉብኝት አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ሲደርሱ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማኔጅመንት አባላት በፖሊሳዊ ሥነ-ሥርዓት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የታጠቃቸውን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅሞችን እና ተቋሙ አሁን የደረሰበትን የለውጥ ደረጃ ፕሬዝዳንቱ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለቱን ሀገራት የፖሊስ ኃይል ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የሱማሊያ ፖሊስ ወጣት መኮንኖች እንዲማሩና እንዲሰለጥኑ ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡትን ጥያቄ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ መቀበላቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ጠንካራ የጋራ የፀጥታ ግብረ ኃይል በማቋቋም በድንበር አካባቢ የጋራ ጥበቃ ለማድረግ እና በሽብርተኝነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መክረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መህሙድ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተከናወነ ባለው ሪፎርም መደሰታቸውንና በተመለከቱት የለውጥ ሥራዎች አድናቆታቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ፖሊስ ልምዱን በማካፈል እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።