3ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር መክፈቻ መርኃ ግብር እየተከናወነ ነው

ጥቅምት 1/2015 (ዋልታ) 3ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር መክፈቻ መርኃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት እየተከናወነ ነው።

“የተቀናጀ የሳይበር ደህንነት ለሃገር ሉአላዊነት” በሚል መሪ ቃል ነው ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር እየተከናወነ ያለው።

በወሩ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ለማህበረሰብ እና ለተቋማት ከሚሰጠው ግንዛቤ ፈጠራ ባሻገር መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነታቸዉን እንዲለዩና እንዲቀንሱ፣ የግሉን ዘርፍ በሳይበር ደህንነት ያለዉን ሚና እና አበርክቶ ከፍ እንዲያደርግ እና የሳይበር ደህንነት ጉዳይ እንደ ወሳኝ ጉዳይ እንዲወሰድ የማስገንዘብና የማበረታታት ስራዎች የሚሰሩበት ይሆናል ተብሏል።

በመርኃ ግብሩ ላይ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የተሰማሩ የግል ተቋማት እና ጀማሪ ኩባንያዎች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የፌደራልና የክልል የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ተመራማሪዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

የሳይበር ወር በወርሃ ጥቅምት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰለ ሳይበር ደህንነት ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ ታሰቦ የሚካሄድ የሳይበር ደህንነት ማስጨበጫ የንቅናቄ መርኃ ግብር እንደሆነም ተገልጿል።

የሳይበር ደህንነት ወር በኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ ነው እየተከበረ ያለው።

በህይወት አክሊሉ