የገንዘብ ሚኒስትሩ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ቡድን አንድ ዋና ዳይሬክተር እና ሌሎች ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

ጥቅምት 3/2015 (ዋልታ) በዋሽንግተን ዲሲ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከዓለም የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ቡድን አንድ ዋና ዳይሬክተር ኢታ ማናቶኮ፣ ከአፍሪካ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አበበ አዕምሮስላሴ እና ከምክትል ዳይሬክተሯ አና ሊሣ ፌዴሊኖ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ከሚሰሩ የልዑካን ቡድን መሪ እና የዴስክ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅትም በኢትዮጵያ እና በድርጅቱ መካከል ያለው ግንኙነት በሚጠናከርበት፣ በተለይም በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መሠረት የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ሽግሽግ ለማካሄድ ከአበዳሪ ሀገሮች ጋር እየተደረገ ያለውን ውይይት በማፋጠን ተጨባጭ ውጤት እንዲኖረው በቀጣይ መከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ገንቢ የሃሳብ ልውውጥ ተደርጓል።

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት የፊስካል ጉዳዮች ዲፓርትመንት ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶች ጋር የኢትዮጵያን የገቢ እና የታክስ አስተዳደር፣ ፐብሊክ ፋይናንስን ማጠናከር ስለሚቻልበት ሁኔታና ይህንንም ለማሳካት በጋራ ስለሚሰሩ የቴክኒክ ድጋፎች እና ትብብሮች ላይ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በውይይቱ ላይም የልዑካን ቡድኑ አባላት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እንዲሁም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሲለሺ በቀለና ሌሎች ባለሙያዎች መሳተፋቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡