ኢትዮጵያ በመጪው ህዳር የምታዘጋጀው የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ተመሰገነ

ጥቅምት 3/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በመጪው ህዳር ወር የምታዘጋጀው የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት አድናቆት ተችሮታል።

የተባበሩት መንግስታት የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ሴክሬታሪያት ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማካሄድ እያደረገች ባለው ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ከጉባኤው አዘጋጆች ጋር ውይይት አድርጓል።

የድርጅቱ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ሴክሬታሪያት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች እና ከኢትዮጵያ የበይነ መረብ አስተዳደር አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጋር ምክክር አድርጓል።

ኢትዮጵያ በመጪው ህዳር ወር ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ኮሚቴዎች ዝግጅት እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል።

በመድረኩ እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ልዑኩ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ዝግጅት ማድነቁም ተመላክቷል።

የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒኤችዲ) ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል።

ልዑኩ በቀጣይ ከኢትዮጵያ የፓርላማ አባላት እና ከዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር አማካሪ ኮሚቴ ጋር እንደሚወያይ ተመላክቷል።