በቀጣዮቹ አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለእርሻ ሥራ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተጠቆመ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) በቀጣዮቹ አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ እየተከናወነ ለሚገኘው የእርሻ ሥራ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩት ከጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ አስከ ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚኖረው የአየር ሁኔታ አዝማሚያ በእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽእኖ አስመልክቶ መረጃ ሰጥቷል፡፡

በዚህም በቀጣዮቹ አስር ቀናት በአብዛኛዎቹ የሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝን የሚጠበቅ ሲሆን ይህም በተለይም በመድረቅ ሂደት ውስጥ ለሚገኙ ሰብሎች አዎንታዊ ጎን ይኖረዋል ማለቱን ኢፕድ ዘግቧል።

ከሚጠናከሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች የተነሳ በአንዳንድ የምዕራብና ደቡባዊ የአገሪቱ አጋማሽ ክፍሎች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ ያስታወቀው የኢንስቲትዩቱ ትንበያ፤ ይህም ለግብርናው ዘርፍ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመላክቷል፡፡