የኢትዮጵያና የሱዳን የመረጃ ተቋማት ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አደረጉ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የሱዳን ሪፐብሊክ አቻው ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር የሚያከናውኗቸውን ሥራዎችና ስምሪቶች አጠናክረው ለመቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በሱዳን ሪፐብሊክ ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል አሕመድ ኢብራሂም ሙፋደል የተመራ የልዑክ ቡድን ዛሬ በተቋሙ ጉብኝት አድርጓል፡፡

ከጉብኝቱ በኋለ በነበረው መድረክም የሁለቱ ሀገራት እንዲሁም የቀጣናውን ወቅታዊ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች የሚመለከቱ አጀንዳዎች ተነስተው ምክክር ተደርጓል፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል ነው የተባለው፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ሱዳን ተመሳሳይ ባህል፣ቋንቋ፣ ሃይማኖት እንዲሁም ሰፊ ድንበር የሚጋሩ በመሆናቸው የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ አድርጎታል፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኘውን ትሩፋት በጋራ በመቋደስም ትስስሩን ለማጠናከር ይሠራል ብለዋል፡፡