ሲሚንቶ ለገበያ የሚያቀርቡ ተቋማት በሚፈልጉት ልክ ምርት እያገኙ አለመሆኑን ቢሮው ገለጸ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) ከፋብሪካዎች ሲሚንቶ ተረክበው በችርቻሮ እና በጅምላ የሚያቀርቡ ተቋማት በሚፈልጉት ልክ ምርት እያገኙ ባለመሆኑ መጠነኛ እጥረት እንዲከሰት ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮ ኃላፊ አደም ኑሪ እንደገለጹት ከጊዜ ወደጊዜ እየናረ የመጣውን የሲሚንቶ ምርት ዋጋ ለማስተካከል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያወጣው የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ በአንፃራዊነት መልካም ወጤቶች የተገኙበት ነበር።

መመሪያው የግንባታ ስራዎች ወጪን ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ የጠቆሙት ኃላፊው፤ በግብይት ስርዓቱ ውስጥ የነበረውን ረዥም ሰንሰለት ለመቁረጥ እና የሲሚንቶ አምራቾች ከተጠቃሚው ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ የሚያስችል ነው ማለታቸውን ኢብኮ ዘግቧል፡፡

በተለይም ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የተባሉ መንግስታዊ የግንባታ ስራዎች፣ ትላልቅ ፋይዳ ያላቸው የግል ግንባታዎች እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ ትስስር መፈጠሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ በዚህም የተሻለ ውጤት መገኙቱን ገልፀዋል።

መመሪያው የልማት ስራዎች እንዳይቆሙ፣ ሰራተኛ እንዳይበተን እና ክንውኑ የታሰበለት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማስቻሉን ጠቅሰው፤  ከዚህ ቀድም በዋጋ ንረት እና በሲሚንቶ እጥረት ይቸገሩ የነበሩ ፕሮጀክቶች አንፃራዊ መሻሻል እንደታየባቸው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ ከእነዚህ ውጪ ላለው የከተማዋ የሲሚንቶ ፍላጎት ከፋብሪካዎች በመረከብ በችርቻሮ እና በጅምላ የሚያቀርቡት የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ድርጅት እና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት መሆናቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል።

እነዚህ የሲሚንቶ አቅራቢዎች አገልገሎት የሚሰጡባቸው ጣቢያቸው ቁጥር አነስተኛ መሆኑ በግብይቱ ላይ ችግር የፈጠሩ ሲሆን ይህም ነዋሪው የሚፈልገውን የሲሚንቶ ፍጆታ ለማግኘት ረዥም ኪሎ ሜትሮች እንዲጓዝ እና ረዣዥም ሰልፎች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ገልፀዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ በቀጣይ ጊዜያት ተቋማቱ ራሳቸውን የማስፋፋትና የማሳወቅ ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ኃላፊው ተናግረዋል።