የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ተቋማት ግባቸውን ለማሳካት ጥሩ ቁመና ላይ መሆናቸውን ያመላከተ ነው ተባለ

ጥቅምት 7/2015 (ዋልታ) የበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት አፈጻጸም ተቋማት ዓመታዊ ግባቸውን ለማሳካት ጥሩ ቁመና ላይ መሆናቸውን እንደሚያመላክት ሚኒስትሮች ገለጹ።

የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩም የተቋማት ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዚህም የሁሉም ሚኒስቴሮች የሦስት ወራት አፈጻጸም በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገመገመ ሲሆን ተቋማቱ ዓመታዊ ግባቸውን ለማሳካት ጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሎጀስቲክስ እንቅስቃሴን ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ፣ የኤክስፖርት ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠርና በብሉ ኢኮኖሚ የተጀመሩ ስራዎችና ሌሎችም የተሳካ ውጤት እንደተገኘባቸው የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል።

በብሉ ኢኮኖሚ በማሪታይም የዓለምን ገበያ ለመቀላቀል ባለሙያዎችን በሀገር ውስጥ በማሰልጠን በውጭ አገራት እንዲቀጠሩ በመደረጉ በዓመት አስከ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የውጭ ምርቶችን አሽጎ በመላክ በቡና የተገኘው ስኬት የላቀ እንደነበር አንስተው በቀጣይ በሌሎች ምርቶችም አፈፃፀሙ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

መሰረታዊ ሸቀጦች ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ሰፊ ተግባራት ማከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ናቸው፡፡

መንግስት ለሀገር ውስጥ ዘይት አምራቾች የምርት ግብአት አቅርቦት 50 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ አምራቾቹ 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በማምረት ለህብረተሰቡ እንዲያከፋፍሉ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በተለይም የነዳጅ ድጎማ ሥርዓቱ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል መደረጉ መንግስትን ከተጨማሪ ወጪ መታደጉን ገልጸዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ጥሩ አፈፃፀም ተመዝግቧል ብለዋል።

በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በሬሚታንስ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ በከተማ ግብርናና ሌሎች አፈፃፀሞች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው አጠቃላይ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ 6 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል።

በትምህርቱ ዘርፍ በሦስት ወራት አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ናቸው።

ትምህርትን ከማስፋፋት፣ የተማሪዎችን ቅበላ ከማሳደግ፣ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ከመቀነስና የትምህርት ቤቶች ምገባን ከማስፋፋት አኳያ የተሻሉ አፈጻጸሞች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡

ከ180 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት ለበጋ መስኖ ዝግጁ ማድረግ መቻሉን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ አይሻ መሀመድ ተናግረዋል።

ለበጋ ስንዴ ልማት የተያዘውን አቅድ ማሳካት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንና በቆላማ አካባቢዎች የአደጋ ምላሽ ስራዎችም በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ በተለይም የመድኃኒትና የህክምና ግብአት አቅርቦትን በሚመለከት ውጤታማ ስራ መከናወኑን የገለጹት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የህክምና ዘርፎችን በማስፋት ሂደትም ከታች ጀምሮ እስከ ስፔሻሊቲ ህክምና እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በወቅታዊ ፈተናዎች ሳቢያ የህብረተሰብ ጤና ችግሮች መኖራቸውን አስታውሰው ለዚህም ድንገተኛ ምላሽ የመስጠት ስራ በስፋት ተከናውኗል ብለዋል።

የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ጠንካራ የጤና ሥርዓት መገንባት በመሆኑ ይህንኑ ለማሳካት ሰፊ ርብርብ ይደረጋል ማለታቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!