በ8 ክልሎች የሚተገበር የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎት ማሻሻያ ኘሮጀክት ይፋ ሆነ

ጥቅምት 11/2015 (ዋልታ) በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ በ8 ክልሎች የሚተገበር የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎት ማሻሻያ ኘሮጀክት ይፋ ሆነ::
አምሪፍ ኼልዝ ኢትዮጵያ እና ጂ ኤስ አይ በተሰኙ አጋር ድርጅቶች ቅንጅት የሚተገበረው ይሄው ፕሮጀክት በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በተመረጡ 14 ወረዳዎች መተግበር ከጀመረ በኋላ በአምስት ዓመታት ውስጥ 30 ወረዳዎችን ጨምሮ በድምሩ 44 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
ከ24ኛው ዓመታዊ የጤና ጉባዔ ጎን ለጎን በሀዋሳ በተካሄደ ፕሮግራም ላይ ይፋ በተደረገው ፕሮጀክት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የዚህ ፕሮጀክት ይፋ መሆን ከአመት በፊት ፀድቆ ወደ ስራ የገባውን የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ የሚያግዝ በመሆኑ አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ የአምሪፍ ኼልዝ አፍሪካ ምክትል ዋና ካንተሪ ዳይሬክተር ዶ/ር ስንታየሁ ፀጋዬ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆን በአገር አቀፍ ደረጃ መንግስት በጤናው ዘርፍ በዋናነትም የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎትን ለማሻሻል እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ያግዛል ብለዋል።
የአምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ዳይሬክተር ተመስገን አየሁ አንደገለፁት ፕሮጀክቱ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚተገበር ከመሆኑም በላይ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ የሚያተኩርና የጤና ተቋማትንና የህብረተሰቡን መደጋገፍ የሚያጠናክር ነው።