መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

 

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት “ሰላም እና ደህንነት በአፍሪካ” በሚል አጀንዳ ላይ ትናንት ዝግ ስብሰባ አካሂዷል።

አምባሳደር ታዬ ስብሰባውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅትም መንግሥት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን መብቶች ለማክበርና ለማስከበር፣ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና ስርጭትን ለማሳለጥ የተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎችን በተመለከተም ማብራሪ ሰጥተዋል።

በትግራይ የሚገኙ ስትራቴጂክ ቦታዎችና ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመቆጣጠር ሕጋዊነትና ተጨባጭ ምክንያትን በተመለከተም ማስረዳታቸውን ጠቅሰዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጉዳይ በመርህ ላይ የተመሰረተ አተያይን እንደሚጠይቅም በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ መንግሥትና የጸጥታ ኃይሎች ትግራይን ጨምሮ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል መንቀሳቀስ ሉአላዊ መብታቸው መሆኑንም ነው ለምክር ቤቱ ያስረዱት።

በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑንም ነው አምባሳደር ታዬ በማብራሪያቸው የገለጹት።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የምክር ቤቱ አባላት ለሂደቱ ስኬት ድጋፍ እንዲያደርጉና በሂደቱ ላይ ጥርጣሬን የሚያጭሩ አቋሞችን ከማንጸባረቅ እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።