ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት ሊደግፍ እንደሚገባ ተገለጸ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) አሜሪካን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታን ለማቅረብ እና አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያደርገውን ጥረት ሊደግፍ ይገባል ሲል አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ (ኤፓክ) ገለጸ።

የኮሚቴው ሰብሳቢ መስፍን ተገኑ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ የሰላም ሂደቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን በጎ ተግበራት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች የጀመረውን ጦርነት በመከላከል በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞችን ከሽብር ቡደኑ ነጻ በወጡ የክልሉ አከባቢዎች ሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ እያደረገ የሚገኘው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ቡድኑ በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንዳይመጣ፤ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው መንግሥት የህዝቡን ሰላም የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ የፈረሱትን የመሰረተ ልማት መልሶ መገንባት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ያሉት ሰብሳቢው መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነት ሊደግፍ የሚገባው በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።