የሕዳሴው ግድብ ለአፍሪካ ሞዴል የሆነና መንገድ ያሳየ ፕሮጀክት ነው ተባለ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕደሴ ግድብ ለአፍሪካ ሞዴል የሆነና መንገድ ያሳየ ፕሮጀክት ነው የአባይ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው 12ኛው “ስለኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ እየተካሄደ ነው።

“ልማት በተግባር ስለኢትዮጵያ” በሚል እየተካሄደ ባለው የፓናል ውይይት ላይ የሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

ዋና ስራ አስኪያጁ በጽሁፋቸው፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ናት፤ ነገር ግን ይህን ሀብቷን በአግባቡ ሳትጠቀምበት ዘመናት ተቆጥረዋል ሲሉ አብራርተዋል።

ሀገሪቱ ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል የውሃ ሀብቷ ተጠቃሽ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ የአባይ ተፋሰስ ብቻ 70 በመቶ የሀገሪቱን የውሃ ሀብት የያዘ ነው ብለዋል።

በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ወንዞች ከከፍተኛ ቦታ የሚፈሱ በመሆናቸው በተለይ ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚውሉ ናቸው፤ ነገር ግን ይህን ሀብት በአግባቡ አሟጥጦ መጠቀም አልተቻለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከውሃ ብቻ 45 ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ትችላለች፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 67 በመቶው ከአባይ ተፋሰስ የሚገኝ ነው ብለው፤ ይህንን ተፋሰስ ማልማት የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ያለውን ችግርም የምንቀርፈው ይህን ሀብት መጠቀም ስንችል ነው ብለዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ወንዞቻችን ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ሀገራቱ ፋይናንስ እንዳይገኝ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በውስጥ ጉዳያችን ገብተው ሳይቀር የተልዕኮ ጦርነት እንደከፈቱብን የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ ኢትዮጵያ ይህን ተቋቁማ ፕሮጀክቷን ከዳር እያደረሰች ትገኛለች ብለዋል።

“የምንሠራው የሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካ ሞዴል የሆነና መንገድ ያሳየ ፕሮጀክት ነው” ሲሉም ነው በግድቡ ዙሪያ የነበሩ ተግዳሮቶችን እና የታለፈባቸውን መንገዶች ከእነ ስኬቱ ያብራሩት።

“ለአፍሪካ ወንድሞቻችን መንገድ እያሳየን ነው፤ የተጀመሩ ውጥኖቻችን ይቀጥላሉ፤ ግድባችን በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተገነባ ነው፤ አሁን ላይ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ ከ86.3 በመቶ በላይ ደርሷል፤ ሁለቱ ተርባይኖቹ ኃይል እያመነጩ ነው” ሲሉም አብራርተዋል፡፡

መንግሥት በከፍተኛ ቁርጠኝነት ባይሠራ እና ፕሮጀክቱን ለማሰናከል ጠላቶቻችን እንደሰሩት ሥራ ቢሆን፣ የአባይ ግድብን እዚህ ደርሶ አናየውም ነበር ብለዋል የግድቡ ሥራ አስኪያጅ።

ይህ ፕሮጀክት በኮንክሪት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ደም ጭምር እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ “በቦንብ ማፍረስ ይቻላል” የሚል ዛቻ ሳይቀር የተሰነዘረበት፤ የግንባታ ግብዓት እንዳይደርስ መንገድ ላይ ማስተጓጎል ብቻ ሳይሆን ሲሚንቶ እንዳይመረት ፋብሪካው አካባቢ ሄዶ የሽብር ሥራ የተሰራበት ፕሮጀክት ቢሆንም፤ በመንግሥት ጥረትና በእየንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ርብርብ እዚህ ደርሷል ብለዋል።

እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች በሌሎች ሀገራት የየሀገራቱን ኢኮኖሚ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ከተው አይተናል፤ በኢትዮጵይል ግን ይህ አልሆነም፤ ምክንያቱም የመንግሥትና የህዝቡ የጋራ ፕሮጀክት እንደመሆኑ፣ በጥበብና በከፍተኛ ቁርጠኝነት የተመራ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡