የኦሮሚያ ክልል 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እያለማ መሆኑን አስታወቀ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ገልፀዋል።

በክልሉ የስንዴ ልማት በ3 ዋና ዋና የትግበራ ምሰሶዎች መደራጀቱን የተቀሱት ርዕሰመስተዳድሩ፤ እነርሱም በመኽር ስንዴ ልማት የመሬት ሽፋንን ማሳደግ፤ የበጋ መስኖ ስንዴን ማስፋፋት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ናቸው ብለዋል፡፡

በትግበራ ምሰሶዎች የተገኙ ውጤቶች ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀው፤ በክልሉ ባለፉት ሶስት አመታት በመኸር ስንዴ ልማት ረገድ የተሰሩ ስራዎች ትልልቅ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሽፋን በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው 7 ሺሕ ሔክታር መሬት በማልማት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አሁን ላይ 1 ሚሊየን ሔክታር ደርሷል ብለዋል፡፡

ክልሉ በበጀት ዓመቱ 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ እስካሁንም ወደ 20 ሺሕ ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በቄለም፤ ምዕራብ ወለጋ፤ ጅማ እና ኢሉ አባቦር ዞኖች ዘር ወደ መዝራት ገብተዋል ያሉት ርዕሰመስተዳድር  ሽመልስ፤ ኦሮሚያ አመቱን ሙሉ ስንዴ የሚዘራበትና የሚታጨድበት ክልል እየሆነ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡

የክልሉን አካባቢያዊ ስነ ምህዳር ግምት ውስጥ ያስገቡ አግባብነት ያላቸውን ዘሮች ለአርሶ አደሮች እንዲጠቀም በማድረግ፤ እንዲሁም መካናይዜሽንን በማስፋፋት ረገድ የተሰሩ ስራዎች ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ የያዘችውን ስንዴ ኤክስፖርት የማድረግ ውጥን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት ክልሉ 74 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ይህንን ያሉት በሀገር አቀፍ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ፕሮግራም ማስጀመሪያ መረሀ ግብር ላይ ነው።

በደረሰ አማረ