ኢትዮጵያ ለኬኒያ ለምትሸጠው የኤሌክትሪክ ሃይል መሠረተ ልማት ግንባታ እየተፋጠነ ነው

ጥቅምት 16/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ለኬኒያ ለምትሽጠው የኤሌክትሪክ ሃይል መሠረተ ልማት ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ በኬኒያ ኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስቴር የካቢኔ ጸሐፊ ሞኒካ ጁማ ገለጹ።

ኢትዮጵያና ኬኒያ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ አሁን ላይ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለመሸጥ የሚያስችላት ሲሆን በቀጣይሞ የአቅርቦቱን መጠን እስከ 400 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጩን የመሠረተ ልማት ግንባታ ሂደት የተመለከተ የስራ ጉብኝት ያካሄዱት በኬኒያ ኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስቴር የካቢኔ ጸሐፊ ሞኒካ ጁማ (ዶ/ር) ግንባታው እየተፋጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኬኒያ ግዛት በኩል የሚገኘው 612 ኪሎ ሜትር የመሰረተ ልማት ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

በግንባታው ሂደት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሙም ስራውን አያከናወኑ የሚገኙት ባለሙያዎች ግን በጥንካሬ እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እያካሔደች የምትገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ለማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ጅቡቲ ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ያካሄደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ስምምነት ፈርማለች፡፡