በምስራቅ ሸዋ ዞን ስንዴን ከ200 ሺሕ በላይ ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱ ተገለጸ

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ስንዴን ከ200 ሺሕ በላይ ሄክታር መሬት በማልማት ከ7 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ፡፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ የተመራ ልዑክ በዞኑ ቦራ ወረዳ ዶዶ አደራ ቀበሌ የመስኖ ስንዴ የመዝራት ስራ አስጀምረዋል።

በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል መንግስት ያቀደውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በምስራቅ ሸዋ ዞን ለስንዴ ምርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛልም ተብሏል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ በዞኑ እስከ አሁን በተሰራ የስንዴ እርሻ ስራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ ቦራ ወረዳ ዶዶ አደራ ቀበሌ በመጀመሪያ ዙር የስንዴ እርሻ ስራ 115 ሺሕ ሄክታር መሬት ለምቶ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል መሰብሰቡን የገለጹት አስተዳዳሪው በዚህ ዓመትም ከ200 ሺሕ በላይ ሄክታር መሬት በማልማት ከ7 ሚሊየን በላይ ኩንታል ስንዴን ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

በዚህ ዓመት ሊፈፀም ከተያዘው እቅድ ውስጥ 1 ሚሊየን ኩንታል በቀጥታ ወደ ውጭ ሀገር የሚላክ መሆኑን ገልጸው ይህም ሀገሪቱ በምግብ ራሷን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ ለመላክ ያቀደችውን እቅድ እንዲሳካ ይረዳልም ነው ያሉት፡፡

ቀሪው 6ሚሊየን ኩንታል የሚሆነው ስንዴም ለሀገር ውስጥ ምግብነት የሚውል መሆኑ ተጠቁሟል።

አስቴር ጌታሁን (ከምስራቅ ሸዋ ዞን)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW