ጀግንነት ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከድል በኋላ ይቅር ማለት ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጥቅምት 24/2015 (ዋልታ) እኛ ጀግኖች ብቻ ሳንሆን ፈጣሪን የምንፈራ ሰዎች ስለሆንን ያገኘነውን የሰላም እድል ተቀብለን እና በሙሉ ልብ ይቅር ብለን የኢትዮጵያን ሰላም እንመልሳልን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አህመድ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ አርባምንጭ ከተማ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ በነበረው የሰላም ንግግር በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች በመሬት ላይ የተገኘውን ድል የሚያስረግጥ የሰላም ድል ተመዝግቧል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፡፡
ከተገኙ ዋና ዋና ድሎች መካከል የኢትዮጵያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም የሚለው መርህ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ማግኘቱ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባለ ቀደምት እና በንግግር የሚያምን ህዝብ ባለበት ሀገር ከአንድ በላይ የመከላከያ ሰራዊት ሊኖር አይገባም የሚለው ሀሳብም በሁለቱም ወገኖች ተቀባይት ማግኘቱ ከድሎቹ መካከል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ ሕግና ሕገ መንግስት መከበር ስላለበት በሕገ ወጥ መንገድ የተደረገው ምርጫ እንዲሰረዝ ከስምምት መደረሱም ሌላኛው ድል ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም አንዳንድ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳይ የሰው ልጆችን ህይወት ሳጠይቁ በሰላም፣ በውይይት እና የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መልኩ ብቻ ምላሽ እንዲያኙ በሁለቱም ወገኖች ከስምምት መደረሱን አንስተዋል፡፡
ባጠቃላይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው ንግግር ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሀሳብ መቶ በመቶ ተቀባይትን ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
ይህ በደቡብ አፍሪካ ያገኘነው ድል ብዙ እጃቸውን ያስገቡ ጠላቶቻችንን ያሳፈረ በመሆኑ ታላቅ ዕድል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን እድል በመቀበል ትግራይን ዳግም በመገንባት እና የትግራይን ህዝብ ወደ ቀደመ ኢትዮጵያዊ ስሜቱ ለመመለስ መላው ኢትዮጵያዊያን እና ወዳጆቻችን ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በነስረዲን ኑሩ