በእስራኤል ምርጫ ቤኒያሚን ኔታንያሁ አሸነፉ

ጥቅምት 25/2015 (ዋልታ) በእስራኤል ምርጫ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በማሸነፍ በድጋሚ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተመልሰዋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ኔታንያሁ በ74 ዓመታት የእስራኤል ታሪክ ለረጂም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም እንኳ በሙስና ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ቢሆንም፣ ይህ ክስ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ተወዳድሮ ከማሸነፍ አላገዳቸውም፡፡

በእስራኤል በአራት አመታት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን ኔታንያሁ እና ወግ አጥባቂ አጋሮቻቸው በሀገሪቱ ፓርላማ ከሚገኙት 120 ወንበሮች 64ቱን ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ከ64ቱ የፓርላማ መቀመጫዎች የኔታንያሁ ሊኩዊድ ፓርቲ በግሉ 32ቱን ሲያሸንፍ የአስራኤል ጽንፈኛ ኦርቶዶክስ ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች አጋሮቹ ደግሞ የተቀሩትን ወንበሮች ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ምርጫውን ኔታንያሁ ቢያሸንፉ ደስተኛ እንደሚሆኑ ሲገልጹ የቆዩት ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ያር ላፒድ ለተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በነስረዲን ኑሩ