ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጥሪ አቀረቡ

ጥቅምት 25/ 2015 (ዋልታ) የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት የሚያጸና በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን ጥሪ አቀረቡ፡፡

የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባላት የስምምነቱን አጠቃላይ ሂደትና ቀጣይ ስራዎችን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ለሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች፣ ለክልል ርዕሳነ  መስተዳድሮች፣ለከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎችና ለብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ስምምነቱ በዋናነት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ የኢትዮጵያ ህዝቦችን የጋራ ጥቅም ባስከበረ መልኩ መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡

በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ሁለት የታጠቀ ሃይል ሊኖር እንደማይችልና ህግ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክበር እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከህገ-መንግስት ውጪ ያሉ እንቅስቃሴዎች ቆመው በትግራይ ክልል በህገ-መንግስቱ መሰረት ምርጫ እኪካሄድ ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ገልጸዋል፡፡

ያለን አማራጭ እና መፍትሄ በጋራ ተሳስሮ መሄድ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ከዚህ አኳያ ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ቀደመው ማህበራዊ ትስስራቸው እንዲመለሱ በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡

ሁለት አመት ባስቆጠረው ግጭጥ የደረሰው ጉዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳት መሆኑን ያብራሩት አምባሳደሩ ከዚህ አኳያ የወደሙ ተቋማትን ጨምሮ የመልሶ ግንባታ ስራዎች በጋራ ርብርብ ሊከናወኑ ይገባልም ብለዋል፡፡

የትስስርና የተግባቦት ስራዎችም የህዝቦችን መጻኢ የጋራ ጉዞ ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም  አስረድተዋል፡፡

ያሉንን አቅሞች በማስተባበር ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በግጭቱ ምክንያት በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሌሎች መስኮች በሀገር ላይ የደረሰውን ጫና በማስተካካል ረገድም በትብብር መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከዚህ ረገድ በተለይ መገናኛ ብዙሃን ቁርሾዎችን ማባባስ ሳይሆን ዜጎች ከችግሩ ተምረው በቀጣይ አብሮነታቸውን አጠናክረው የሚሄዱበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በግጭቱ የተጎዳችው የጋራ ሀገራችን ናት ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመሆኑም ስምምነቱ በሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ እድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሰላም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላትን ደግሞ በጋራ ማስቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ ለስምምነቱ ተግባራዊነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡