የአርቲስት አሊ ቢራ ሥርዓተ ቀብር በብሄራዊ ጀግና ደረጀ ይፈጸማል

ጥቅምት 28/2015 (ዋልታ) የአንጋፋው አርቲስት አሊ ቢራ ሥርዓተ ቀብር በብሄራዊ ጀግና ደረጀ የሚፈፀም መሆኑ ተገለጸ፡፡

አርቲስት አሊ ቢራ ባጋጠመው የጤና እክል ምክንያት በአዳማ ጄነራል ሆስፒታል ለሳምንታት የሕክምና ክትትል ሲደረግለት መቆየቱ ታውቋል።

አርቲስቱ በ72 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ከ50 ኣመታት በላይ አገልግሏል፡፡

አርቲስት አሊ ቢራ የዜማና የግጥም ደራሲ ሲሆን ሙዚቃን ያቀናብር እንደነበረም ስለሱ ግለታሪክ የተሰነዱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አንጋፋው አርቲስት ዘመናዊ የኦሮምኛ ዘፈኖችን ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም በማስተዋቅ ይታወቃል፡፡ አሊ ከኦሮምኛ በተጨማሪ በአማርኛ እና በአድርኛ ዘፈኖች እንዳሉት ይታወቃል፡፡

ትውልድ ተሻጋሪ በሆኑ የሙዚቃ ስራዎቹ አሊ ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ መሆኑን ለማረጋገጥ ችሏል፣ ቋንቋ ሳያግዳቸው ብዙዎች የሱን የሙዚቃ ስራዎች  አብረውት አዚመዋልና፡፡

ቤተሰቡ የሰጠው ስም አሊ መሐመድ ሲሆን አሊ የሚታወቀው አሊ ቢራ በሚለው የመድረክ ስሙ ነው፡፡  “ቢራ” የሚለው የኦሮንኛ ቃል የተወሰደው አሊ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ ካቀረበው ዘፈን፣ “ቢራ ዳ ባሬ” ከተሰኘው ዘፈኑ እንደሆነ ይነገራል።

አሊ መስከረም 18 1943 ዓ.ም ድሬ ዳዋ ከተማ መወለዱን ስለሱ ግለ ታሪክ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ለቤተሰቦቹ እና ለአድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።