ክልሉ ስምምነቱ ተፈጻሚ ሆኖ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

ጥቅምት 29/2015 (ዋልታ) የተደረሰውን የሠላም ስምምነት ተፈጻሚ ሆኖ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ክልላችን አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት አስታወቀ።
የክልሉ መንግሥት በመንግሥትና ህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁሟል።
በመንግስትና በህወሓት መካከል ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረውን ጦርነት ለመቋጨት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተደረገው የሠላም ስምምነት በሀገራችን ውስጥ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ሚናው እጅግ የጎላ ነው ሲል ጠቁሟል።
ጦርነት ጎጂና የማያስፈልግ መሆኑን የጠቀሰው ይህ መግለጫ፤ በተለይም በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የሚደረግ ጦርነት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ከማስከተሉም በላይ በህዝዘቦች መካከል መቃቃርን የሚፈጥርና መልሶ ለመጠገን ጊዜ የሚወስድ መሆኑን በመረዳት ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሠላም መስፈን በዓለም አቀፍ መድረኮች በተከታታይ ድምጿን ስታሰማ መቆየቷንም አስታውሷል።
በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ጦርነቱ ቆሞ ዘላቂ ሠላም እንዲወርድ የተደረሠው ስምምነት ከምንጊዜውም በላይ በችግር ውስጥ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን የሠላምና ተስፋ እንዲፈነጥቅ የሚያደርግ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
የሠላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሀገራችንን ወደ ሰላም የመመለስና በጦርነቱ ወቅት የደረሰውን ማህበራዊ ስነልቦና የመጠገን እና ቁሳዊ ጉዳት በመልሶ ግንባታ በመተካት የማቋቋም ኃላፊነት እንዳለበት አመላክቷል።
መግለጫው አያይዞም አሁንም ቢሆን የሀገራችንን ሠላምና የሕዝቦቿን አንድነት የማይሹ ጥቂት አካላት የሰላም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ሴራ በመከላከል በሁለቱ ወገኖች የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን በተገቢው መንገድ መወጣት ይጠበቅብናል ብሏል።
ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖቻችን ከፍተኛ የሆነ ጉዳት አስተናግደዋል፡፡ ጉዳቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ በግጭቱ የወደሙ ተቋማትን ጨምሮ በሌሎች የመልሶ መገንባት ተግባራት ላይ ተዋናይ በመሆን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ስናደርግ እንደነበረው ድጋፍ በመልሶ ግንባታውም የተጠናከረ ርብርብ እንደምናደርግ ለመግለጽ እንወዳለንም ብሏል ክልሉ።