ኅዳር 5/2015 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያን ተደራሽ ከማድረግ ረገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመላከተ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የዲጅታል መታወቂያን በሚመለከት በተመራለት ረቂቅ አዋጅ ላይ የተለያዩ ግብአቶችን ለማግኘት እንዲያስችለው ከአስረጂዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያ የከተማውንም ሆነ የገጠሩን ማህበረሰብ ባማከለ መልኩ ተደራሽ እንዲሆን በአዋጁ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ማስቀመጥ እና የሁሉም ዜጎች መረጃ ወደ አንድ ቋት ከተሰበሰበ በኋላ ለታሰበው ዓላማ መዋል አለመዋሉን የሚያረጋግጥ ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ አስገንቧል፡፡
ከተጠያቂነትም ሆነ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ በአዋጁ በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል ያለው ቋሚ ኮሚቴው ከመረጃ ሚስጢራዊነት ጋር ተያይዞ የተጠያቂነት ጉዳይም በአዋጁ በግልጽ ሊመላከት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው አያይዞም ወንጀልን ከመከላከል እና ሙስናን ከመዋጋት አንጻር በአዋጁ በዝርዝር ሊካተት እንደሚገባ አንስቶ ከሌሎች የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ጋርም ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡
የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ዮዳሄ አርአያስላሴ በበኩላቸው ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ወጪ ቆጣቢ እና በራስ አቅም የዳበረ አስተማማኝ ሲስተም መዘርጋቱን አንስተው ከተደራሽነት አንጻር በተያዘው ዓመት ከ12 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ተደራሽ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠትና ሚስጢራዊነትን ካለመጠበቅ ከሚመጣ ችግር አንጻር ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ድንጋጌ በአዋጁ እንዲኖር ለቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ማቅረባቸውንም አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል አንድ ሰው ዲጂታል መታወቂያ ሲኖረው የደህንነት ስጋት እንደሚቀንስ አስረድተው አዋጁ ለወንጀል መከላከል እና ለሀገራዊ ደህንነት ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡