ከንቲባ አዳነች የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀመሩ

ኅዳር 8/2015 (ዋልታ) “በጎ ፈቃደኝነት ለማህበራዊ መስተጋብር” በሚል መሪ ሃሳብ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀምረዋል።

አገልግሎቱ በክረምት ወራት የተጀመረውን በጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋ ወራት በስፋት ለመጠቀም ያስችላል፡፡

ባለፈው ክረምት በተሰሩ የክረምት የበጎ ፈቃድ ስራዎች 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የመንግስት ወጪ ማዳን መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

አሁን በተጀመረው የበጋ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ለማዳን ታቅዷል።

በበጋው የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ማዕድ ማጋራት፣ ህጻናትና አረጋዊያንን መንከባከብና የተተከሉ ችግኞችን መከታተልና የመንከባከብ ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡

በተጨማሪም በጎነት በትምህርት ቤትና ጤና ለሁሉም በሚል የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል።

በተስፋዬ አባተ