በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተፈናቀሉ ዜጎች የ590 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ590 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ።

የድጋፍ ርክክቡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በተገኙበት ዛሬ በሚኒስቴሩ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተከናውኗል፡፡

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ሰብዓዊ ድጋፍ ብቻ አለመሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ዜጎች አካባቢያቸውን ለመለወጥ፣ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እና ጠንካራ ኢኮኖሚን በመገንባት ከተሞችን ለመቀየር የሚያስችል አቅምን የሚፈጠር መሆኑን ተናግረዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩለቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ያደረገው ድጋፍ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው አስታውሰዋል፡፡

ድጋፉ ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በቁርጠኝነት እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት ኃላፊ መኮንን ያኢ የድጋፍ ፕሮጀክቱ በመደበኛና በአስቸኳይ ጊዜ ለከተሞች በተለያዩ ምክንያቶች ለሚከሰቱ ችግሮች ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተሞች የልማት ሴፍትኔት ድጋፍ የተደረገው ፕሮጀክት ሰው ተኮር የሆነና በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በትላንትናው ዕለት በአፋር ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች የ170 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW