እሁድ ዕለት ለሚካሄደው ታላቁ ሩጫ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ይፋ አደረገ፡፡

በዕለቱ መነሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ የሚጀመረው ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም፣ በቡናና ሻይ፣ በባልቻ መታጠፊያ፣ በጌጃ ሰፈር፣ በ5ኛ መስቀለኛ፣ በአረቄ ፋብሪካ፣ በሜክሲኮ፣ በሰንጋ ተራ፣ በብሄራዊ ቴአትር፣ በሃራምቤ ሆቴል፣ በፍል ውሃ፣ በካዛንቺስ፣ በኡራኤል ቤተክርስቲያን ወደ ባምቢስ ታጥፎ መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደርጋል፡፡

በመሆኑም ሩጫው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር እና አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን መጠቀም እንዲችሉ ለተሸከርካሪ ዝግ የሆኑ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ፦
• ኮመገናኛ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ 22 እና ዘሪሁን ህንፃ
• ከቦሌ መድሃኔአለም ወደ ቅዱስ ኡራኤል ቤ/ክርስቲያን የሚወሰወደው መንገድ አትላስ መብራት
• ከወሎ ሰፈር ወደ መስቀል አደባባይ ኦሎምፒያ ላይ

  • ከጎተራ ማሳለጫ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ለከባድ መኪና አጎና ሲኒማ እንዲሁም ለቀላል ተሽከርካሪ የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አጠገብ
  • ከጎፋ በቂርቆስ አዲሱ መንገድ ወደ ለገሃር ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ መስቀለኛው ላይ
  • ከቡልጋሪያ ማዞሪያ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ የሚወስደው መንገድ ለከባድ ተሽከርካሪ ቡልጋሪያ ማዞሪያ እንዲሁም ለቀላል ተሽከርካሪ ገነት ሆቴል አጠገብ
  • ከሳር ቤት ወደ ሜክሲኮ አፍሪካ ህብረት አካባቢ ትራፊክ መብራት ላይ
  • ከልደታ ፀበል ወደ ቅድስት ልደታ ቤ/ክርስቲያን የሚወስደው መንገድ ልደታ ፀበል አካባቢ
  • ከጦር ሃይሎች ወደ ሜክሲኮ የሚወስደው መንገድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ኑር ህንፃ አካባቢ
  • ከፈረሰኛ ወደ ጌጃ ሰፈር ፈረሰኛ መብራት ላይ
  • ከሞላ ማሩ ወደ ጌጃ ሰፈር ሞላ ማሩ
  • ከበርበሬ በረንዳ ወደ 5ኛ በርበሬ በረንዳ አካባቢ
  • ከጥቁር አንበሳ ሼል ወደ ኢሚግሬሽን ጥቁር አንበሳ ሼል
  • ከሜትሮሎጂ ወደ ፖስታ ቤት ሜትሮሎጂ አካባቢ
  • ከጎማ ቁጠባ ወደ ብሄራዊ ቴአትር ጎማ ቁጠባ አጠገብ
  • ከጎማ ቁጠባ ወደ አረቄ ፋብሪካ እና ሰንጋተራ የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ አጠገብ
  • ከቸርችል ጎዳና ወደ ለገሃር የሚወስደው መንገድ አገር አስተዳደር መብራት ላይ( ኢሚግሬሽን አካባቢ)
  • ከንግድ ማተሚያ ቤት ወደ ፍልውሃ የሚወስደው መንገድ ንግድ ማተሚያ ቤት አካባቢ
  • ከአራት ኪሎ ወደ ውጭ ጉዳይ የሚወስደው መንገድ ፓርላማ መብራት እና አሮጌው ቄራ መታጠፊያ ላይ
  • ከሴቶች አደባባይ ወደ ካዛንቺስ እና ወደ ቶታል የሚወስደው መንገድ ሴቶች አደባባይ አካባቢ

ከለሊቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ውድድሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ፡፡

በተጠቀሱት መንገዶች ላይ ከዋዜማው ምሽት ጀምሮ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድና ማሳደር የተከለከለ መሆኑን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የውድሩሩ ተሳታፊዎች ወደ ሚያልፉባቸው መንገዶች ተሽከርካሪ ይዞ መውጣት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ተገንዝበው አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ለፀጥታ አካላት ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙትም ሆነ ለፖሊስ መረጃ ለመስጠት ሲፈልግ 011-1-11-01 11 እና በ991 ነፃ የስልክ ቁጥሮች መጠቀም እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡