በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን 3ኛውን የኢትዮጵያ ቀን በአቡዳቢ ከተማ አከበሩ

ኅዳር 11/2015 (ዋልታ) በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሦስተኛውን “የኢትዮጵያ ቀን” በአቡዳቢ ከተማ አክብረዋል።
በበዓሉ ላይ በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ቀን በዓል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት በሰላም ስምምነት በታሰረበትና በመላው ሀገራችን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ተስፋ በታየበት ወቅት ለየት ባለ ሁኔታ እየተከበረ ያለ በዓል ነው ብለዋል።
ይህ ሰላም ዘላቂ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላትም ዜጋዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በሀገራቸው ልማት ንቁ ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቅሰው በ”ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” እና “ከኢድ እስከ ኢድ” ጥሪዎች ወቅት ያደረጉት ተሳትፎ ከፍ ያለ እንደነበር አንስተዋል።
በዓሉ የእግር ኳስ ውድድር፣ የሙዚቃ ዝግጅት፣ ፋሽን ሾው፣ ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢ የተዘጋጀ የሎተሪ ዕጣ የማውጣት ሁነቶችን ያካተተ እንደነበርም ተጠቁሟል።