ተቋማቱ መረጃ ለመለዋወጥ እና በጋራ ለመስራት የሚስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራራሙ

ኀዳር 12/2015 (ዋልታ) በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ ከሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አህመድ ኢብራሂም አሊ ሙፍዲል እና ሌሎች ከፍተኛ የተቋሙ አመራሮች ጋር በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በካርቱም መክረዋል።

አገልግሎቱ ለዋልታ በላከዉ መረጃ ከውይይቱም በኋላም ሁለቱ ተቋማት የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መረጃ ለመለዋወጥ እና በጋራ ለመስራት የሚስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል ።

የስምምነቱ ትኩረትም ተቋማቱ በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሞክሮ እና መረጃ ለመለዋወጥ፣ የቀጠናው የጋራ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት በጋራ መዋጋት ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል፣ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ ደህንነትን ማረጋገጥ እና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ሰላም የሚጎዱ አካላትን በጋራ መከላከል ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።

የልዑካን ቡድን በካርቱም ለሁለት ቀናት በነበረው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ከሱዳን ልአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታ አልቡራህምንና ከልአላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ሞሐመድ አምዳን ዳጋሎ ጋር ተገናኝተዉ በሁለቱ ሀገራት ሰላምና ደኀንነት ዙሪያ መወያዩቱን ተመላክቷል።