በመቐለ ከተማ የባንክ እና የስልክ አገልግሎት በሚቀጥለው ሳምንት እንደምጀምር ተገለጸ

ታኅሣሥ 17/2015 (ዋልታ) በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የባንክ እና የስልክ አገልግሎት በሚቀጥለው ሳምንት እንደምጀምር ተገለጸ፡፡

በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት በሰላም እንዲጠናቀቅ የፌዴራሉ መንግስት ከህወሓት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት የተኩስ አቁሙን ተከትሎ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን የፌዴራሉ መንግስት ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።

በዚህም ኢትዮ ቴሌኮም 27 የሚደርሱ የትግራ ከተሞች ላይ የስልክ አገልግሎት ያስጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም መቐለን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ትልልቅ ከተሞች የኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል።

ወደ መቐለ ያመራው የፌዴራሉ መንግስት ልኡክ ለትግራይ ህዝብ እንዳረጋገጠው በክልሉ ትልቅ ችግር የሆነው የባንክ አገልግሎት በቅርቡ ይፈታል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 18 ባለሙያዎችን ወደ መቐለ እንዳሰማራ የጠቀሱት የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ባንኩ የሚስተካከሉ የሲስተምና የኦዲት ስራዎችን በዚህ ሳምንት አጠናቆ አገልግሎት ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ህብረተሰቡ ለከፋ ችግር እንደተዳረገ እንረዳለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህንን ችግር በአጭር ጊዜ ለመፍታት ከዛሬ ጀምሮ ባለሙያዎቻች ወደ ስራ ማለታቸውን የኢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።