ታኅሣሥ 26/2015 (ዋልታ) የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በከፍተኛ ጽናት ትምሀርቱን በመከታተል 37 A+ ውጤት በማምጣት ለተመረቀው ለተማሪ ግርማ ዳባ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል ሰጠ፡፡
ተማሪዉ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ረዳት መምህር ሆኖ እንዲያገለግልም ውሳኔ መተላለፉን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል፡፡
በወላይታ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስና ህክምና ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ዲን ሀይሉ ጫኔ (ረ/ፕ) ለዋልታ እንደገለፁት በትምህርት ቤታችን የወርቅ ተሸላሚ የነበረው ተማሪ ግርማ ዳባ በዩኒቨርስቲው የትምህርትና የስራ ዕድል ተመቻችቶለታል ብለዋል፡፡
የትምህርት ክፍል ዲኑ አያይዘዉም የረዳት መምህርነት ዕድል ተሰጥቶት በዩኒቨርስቲው ውስጥ ስራ የሚጀመር መሆኑንና ሁለተኛ ዲግሪውን የሚቀጥልበት የነፃ ትምህርት ዕድል ማመቻቸታቸውን ገልፀዋል፡፡
የወላይታ ዩኒቨርስቲ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ሀለተኛ ዲግሪ የሚሰጠው ባለው ክፍት ቦታ መሰረት የነበረ ቢሆንም ለተማሪ ግርማ ዳባ ግን በምርጫው እንዲሆንና የፈለገውን እንዲማር ከውሳኔ መድረሱንም ዲኑ አስታውቀዋል፡፡
ተማሪ ግርማ ዳባ ለትምሀርት ልዩ ትኩረት በመስጠት በፈተናዎች ሳይበገር ስኬት ማስመዝገቡ ለበርካታ ወጣቶች ምሳሌ የሚሆንም ነው ብለዋል፡፡
ዋልታ ቲቪ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ደረጃ ግንባር ቀደም ነዉ ያሉት ዲኑ እንዲህ አይነት የህይወት ተሞክሮ ሌሎችን የሚያስተምርና የሚያበረታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ተማሪ ግርማ ዳባ ባጋጠመው የህይወት ውጣ ውረድና የጤና እክል ከጉዞው ሳይሰናከል 37 A+ በማምጣት ከወላይታ ዩኒቨርስቲ በማዕረግ መመረቁን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
በሳሙኤል ሙሉጌታ