በሀረሪ ክልል በጤና መድህን የተገኙ ውጤቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ጥር 1/2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የአባላት እድሳትና ምዝገባ በይፋ ተጀምሯል።

በብልፅግና ፓርቲ ሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱጀባር መሀመድ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ የተገኙ ስኬቶች ማጠናከር እና ሁሉን አቀፍ የጤና መድህንን ተደራሽ ለማድረግ የበለጠ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በተለይም በሚቀጥሉት ወራት ህብረተሰቡን የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አርጋው ሀረሪ ክልል ለጤና መድህን አገልግሎት ትኩረት ከተሰጠባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው መክፈል ለማይችሉ ዜጎች የጤና አገልግሎት በመስጠት ፍትሃዊነትን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው በክልሉ እስካሁን ድረስ 45 ሺሕ 539 አባዎራዎችና እማዎራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የጤና መድህን አገልግሎቱ ድንገተኛ ወጪ መቀነስ፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ እና የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት በማጎልበት አስተዋፅዕ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም እናቶችና ህፃናት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንና በክልሉ የጤና አገልግሎት እንዲሻሻል እያገዘ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በቂ ህክምና ያለማግኘት ችግር መቅረፉንና በጤና ችግር ምክንያት የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲቀንስ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)