ሚኒስቴሩ ከተሞች መሬታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ መሰራቱ ገለጸ

ጫልቱ ሳኒ

ጥር 15/2015 (ዋልታ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ከተሞች ያላቸውን የመሬት ሀብት በመመዝገብ በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ መሰራቱን ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ የ2015 ግማሽ በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

ሚኒስቴሩ በግማሽ በጀት ዓመቱ በመንግስት አስተባባሪነት የቤቶች ግንባታ ማከናወኑን ገልጾ የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን አስታውቋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ከተሞች ያላቸውን የመሬት ሀብት በመመዝገብ መሬታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮማቴ በበኩሉ የህብረተሰቡን የቤት ጥያቄ ለመፍታት ምን ታቅዷል? ህገወጥ ግንባታና መሬት ወረራን ለመከላከልስ ሚኒስቴሩ ምን እየሰራ ነው? የሚል ጥያቄ አንስቶ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ እና ሚኒስትር ዴኤታዉ ፈንታ ደጀን የህብረተሰቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከህገወጥ ግንባታና መሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የተቆጣጣሪዎች ቸልተኝነት እና ጨለማን ተገን አድርጎ ቤት የመገንባት ሂደቶች እንዳሉ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ስራ እሰራለሁ ብሏል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በቀሪው ግማሽ  በጀት ዓመት ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚንቀሳቀስ አስታውቋል።

በሱራፌል መንግስቴ