የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የማስተባበሪያ ፅ/ቤት ለመክፈት ስምምነት ተፈራረመ

የካቲት 10/2015 (ዋልታ) የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

 

ስምምነቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ፀሃፊ ማማዱ ቢትዬ ጋር ተፈራርመዋል።

 

መቀመጫውን በዙምባቡዌ ያደረገው ፋውንዴሽኑም በኢትዮጵያ የማስተባበሪያ ፅ/ቤት ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

 

እ.ኤ.አ በ1991 ምስረታውን ያደረገውን የአፍሪካ ህብረት አንድ አካል የሆነው የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የማስተባበሪያ ፅ/ቤት መከፈት ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ የሚያያደርግ ይሆናል ነው የተባለው።

 

በተጨማሪም የፅ/ቤቱ በኢትዮጵያ መከፈት የመንግስት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተደራሽነት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ እና ቅልጥፍናን መሰረት ያደረገ አገልግሎትን እንዲሰጡ የሚያግዝ መሆኑንም ተገልጿል።

 

በአባል ሀገራቱ መካከል እድገትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለማገዝ ከ2023 ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚቆይ ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱም ተመላክቷል።

በሔብሮን ዋልታው