በሀረር ከተማ የተንቀሳቃሽ ቅርሶች አውደርዕይ ተከፈተ


የካቲት 17/2015 (ዋልታ) በሀረር ከተማ “ቅርሶቻችን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት” በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከሀረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ተንቀሳቃሽ የቅርሶች አውደርዕይ ተከፈተ።

የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ አብዶሽ እንደተናገሩት ከፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በቅንጅት መሰራቱ ሀረር ከተማ የሚገኙ ቅርሶችን በዘመናዊ መንገድ ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እገዛ ያደርጋል።

የአውደርዕዩም ህዝቡ በሀገሪቱ ያሉ የአርኪዮሎጂ ውጤቶች እንዲያውቅ ከማድረግ ባለፈ ወደ ከተማው የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲያድግ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የብሔራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር ደምረው ዳኜ በበኩላቸው የአውደርዕዩ ዋና ዓላማ የሙዚየሞች የሚገኙ እንቅስቃሴ ማስቃኘት እና ሉሲን ጨምሮ የሀገሪቱ የሚገኙ ቅርሶች ህብረተሰቡ በተለይም ተማሪዎች እንዲያውቋቸው ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዋናነት አሉታዊ ተፅዕኖ ካሳደረባቸው ተቋማት መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ መሆኑን ጠቁመው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በወረርሽኙ ምክንያት የተንቀሳቃሽ ሙዚየም አውደርዕይ እንቅስቃሴ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አውደርዕዩ ከ2012 ዓ.ም ወዲህ የተከፈተ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰው ይህም የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች መሰል ስራዎች እንደሚከናወኑ የተጠቆመ ሲሆን ለአምስት ተከታታይ ቀናት ክፍት በሆነው ኤግዚቢሽን ሉሲን (ድንቅነሽ) ጨምሮ በሀገሪቱ የሚገኙ የሰው ዘር ግኝቶች ለእይታ ቀርበዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)