የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግና ለማጠናከር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገለጸ

አኪንውሚ አዴሲና

የካቲት 18/2015 (ዋልታ) የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግና የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማጠናከር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና ገለጹ።

ባንኩ የኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማገዝ የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ የግብርና ምርታማነትን ለሚያሳድጉ የአግሮ ኢንዱስትሪ ማቀነባበሪያና ለግብርና ምርት እሴት ልዩ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በኃይል ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት ባንኩ እየደገፈ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ የመጣውን የግብርና ዘርፍ በመደገፍ አኅጉሪቷ የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ዘርፉም እድገት እያሳየ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቆላማ አካባቢዎች እያካሄደች የምትገኘውን የስንዴ ምርታማነት ግቡን እንዲመታም ባንኩ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

በተለይም በተሰራጨው የተሻሻለ የስንዴ ዝርያም ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትና ምርታማነቷን በመጨመር የሚበረታታ ስራ መስራቷን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።