ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለህዝብ አንድነትና ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

የካቲት 27/2015 (ዋልታ) ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀሳብ እና ተግባር በመስማማት ለአገር እና ህዝብ አንድነትና ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

በአገር ሰላም ግንባታ፣ በአገራዊ ምክክር እና አንድነት ዙሪያ የወጣቱን ሚና ለማሳደግ ያለመ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

ውይይቱን ያዘጋጀው ኢንስፖየርድ ኢትዮጵያን ዩዝ ከኦክስፋም፣ ሰላም ሚኒስቴር እና የሰራተኛ እና ማህበራዊ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው ተብሏል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ያለ ሰላም አንድነት፤ ያለ መግባባት ደግሞ ሰላም ሊመጣ እንደማይችል እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀሳብ እና በተግባር በመስማማት ለአገር እና ህዝብ አንድነትና ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጄን ቤከር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፍታቱ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው አገራዊ ምክክር እና የጋራ በመግባባት ግጭቶችን ለመፍታት ቀዳሚ መፍትሄ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በበኩላቸው በሰላም ግንባታው ሂደት በርካታ ግብአቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸው ምክክሩ በክልልና አገር አቀፍ ሀሳቦች እና ፍላጎቶች ላይ በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል።

ሰላም እና መረጋጋት ለማህበረሰባችን በተለይ ደግሞ ለሴቶች፣ ወጣቶች እና ህፃናት አስፈላጊ በመሆናቸው በጋራ መግባባት ሰላማዊ አገር የመገንባት የጋራ ኃላፊነት አለብን ሲሉም አክለዋል፡፡

በቁምነገር አሕመድ