ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለቦንጋ ከተማ ቀላል የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ

የካቲት 28/2015 (ዋልታ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የቦንጋ ከተማ ቀላል የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ቀዳማዊት እመቤተ ዝናሽ ታያቸው ከጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጋር በመሆን ቦንጋ ከተማ ገብተዋል።

እንዲሁም በቦንጋ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ያስገነባው የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ ተመርቋል።

ፋብሪካውን ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው መርቀው የከፈቱት ሲሆን በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ነጋሾ ዋጌሾን (ዶ/ር) ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ፋብሪካው በቀን ከ42 ቶን በላይ የስንዴ ዱቄትና ከ300 ሺህ በላይ ዳቦ ማምረት እንደሚችል ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ1 ሄክታር መሬት ላይ ስራ የጀመረው ይህ የስንዴ ዱቄትና ዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታው በ 11 ወራት ውስጥ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የዳቦና ዱቄት ፋብሪካው የሚስተዋለውን የዳቦ እጥረት በመቅረፍና እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ሥራ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።

ፋብሪካው ከመቶ ሃምሳ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በ11 ከተሞች ተመሳሳይ የማምረት አቅም ያላቸው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎችን በጋራ ለመገንባት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ከተፈራረመ በኋላ ለምረቃ ከበቁ ፋብሪካዎች መካከል ዛሬ የተመረቀው አንዱ ነው።