ኢትዮጵያ ሴቶች በአገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተካፋይ የሚሆኑባት እና ሃሳባቸው የሚሰማባት እንድትሆን እንትጋ – ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

የካቲት 29/2015 (ዋልታ) የምንገነባት ኢትዮጵያ ሴቶችና ታዳጊ ሴት ልጆች ሴት በመሆናቸው በራሳቸው በመተማመናቸው የማይሸማቀቁባት፣ በአገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተካፋይ የሚሆኑባት ፣ ሃሳባቸው የሚሰማባት እንድትሆን ሁላችንም እንትጋ ሲሉ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የ2015 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም “በመላው አገራችንና በውጭ አገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ሴቶች እንኳን ለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በደህና አደረሰን” ብለዋል።

ሁሌም እንደምለው የሴቶች ቀን በዓመት አንድ ቀን የሚታወስ ሳይሆን የ365 ቀናት ሥራ መሆን አለበት ያሉት ሲሆን ያለፍነውን፣ እየኖርን ያለነውንና የወደፊቱን ከሴቶች እኩልነት፣ ተጠቃሚነት ከሰው ልጅ መብት አንጻር እንድንቃኝ አስታዋሻችን፤ የማንቂያ ደወላችን ነው ብለዋል፡፡

በሴቶች ላይ ከሚደርሰው የችግር አዙሪት ለመውጣት ቁልፍ ጉዳይ የሴቶች መደራጀት ጠቅሰው፣ የመብት ትግል የተናጠል ትግል ስላልሆነ ሴቶች ጠንካራ የጋራ አጀንዳ ሊይዙ ይገባል፡፡

የሴቶች አጀንዳ የሕዝብ ጉዳይ እንዲሆን የሚሰራ፣ መፍትሔ የሚያፈላልግ፣ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ እውቀትና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለዚህ ዓላማ የሚያስተባብር ጠንካራ ማህበር እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡

ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለንን ትስስር ለማጠናከር ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተው “የአፍሪካ ሴት መሪዎች ጥምረት “AWN” የኢትዮጵያ ቅርንጫፍን ማጠናከርና የልምድ ልውውጦችን ማጎልበት ይጠበቅብናልም ነው ብለዋል፡፡

ይህንን የሴቶች ወር በማስመልከት ያለፈውን እንድንገመግም፣ የዛሬውን በርትተን እንድንሠራና የወደፊቱን እንድናቅድ ቆም ብለን እንድናስብ ለሁሉም አደራ ማለት እፈልጋለው ያሉት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የምንገነባት ኢትዮጵያ ሴቶችና ታዳጊ ሴት ልጆች ሴት በመሆናቸው፣ በራሳቸው በመተማመናቸው የማይሸማቀቁባት፣ በአገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተካፋይ የሚሆኑባት ፣ ሃሳባቸው የሚሰማባት እንድትሆን ሁላችንም እንትጋ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።