ዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀን እየተከበረ ነው

የካቲት 29/2015 (ዋልታ) የዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 “ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት” በሚል መሪ ሀሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ47ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።

መሪ ቃሉ ሁሉን አካታች የዲጂታል አገልግሎትን ለማስፋት የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ላይ መስራት በማስፈለጉ ነው የተመረጠው፡፡

ቴክኖሎጂን በመጠቀም የፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ዙሪያ በስፋት መስራት እና የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን በማዳበር በሴቶች የኢኮኖሚ አቅምን የማመጣጠን ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሴቶች የበይነመረብ ተደራሽነት መስፋት እንደሚያስፈልግ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

አሁን ባለንበት የዲጂታል ዓለም የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑን የጠቆመው የተባባሩት መንግስታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም በሰው ሰራሽ አስተውሎት መስክ የተሰማሩ ሴት ሰራተኞች 22 በመቶው ብቻ እንደሆነ አመላክቷል፡፡

በ 133 የኢንዱስትሪዎች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስርዓት ላይ በተደረገ ጥናት 44 ነጥብ 2 በመቶ የስርዓተ-ፆታ አድሏዊነት ያሳያል።

በዘንድሮው የሴቶች ቀን መንግስታት የግሉ ሴክተር እና ማህበረሰብ አንቂዎች የሴቶች ተሳትፎ በመጨመር እና አቅም በማጎልበት ለሴቶች ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት እንዳለባቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡