ሩሲያ በበርካታ የዩክሬን ከተሞች ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈፀመች


የካቲት 30/2015 (ዋልታ) ሩሲያ በበርካታ የዩክሬን ከተሞች ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈፀሟ ተሰማ፡፡

ሚሳኤሎቹ በዩክሬን ከሰሜን ካርኪቭ እስከ ደቡባዊው ኦዴሳ እና ምዕራብ ዘሂቶሚር ከተሞች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ላይም የሚሳኤል ጥቃት ሰንዝራለች ነው የተባለው፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የዩክሬን ጦር ሩሲያ 81 ሚሳኤሎችን በበርካታ ከተሞች ላይ ማስወንጨፏን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ስምንት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በጥቃቱ ላይ መሳተፋቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ጥቃትን ተከትሎም የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተቋርጧል፡፡

የምስራቃዊቷን የባኽሙት ከተማ ለመቆጣጠር የሞት ሽረት ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን የሩሲያ ኃይሎች ከተማዋን በከፊል መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡