የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኮሚሽኑ የሚያከናወናቸውን ስራዎችና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፉ ገለጹ

መጋቢት 9/2015 (ዋልታ) የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሚያከናወናቸውን ተግባራትና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፉ ገለጹ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከአይ.ኦ.ኤም የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ተጠሪ መሐመድ አብዲከር ጋር በተሃድሶ ኮሚሽን ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂደዋል።

አምባሳደሩ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አላማ በሰላም ስምምነቱ መሰረት ትጥቅ የፈቱ እና በሕጋዊ የምዝገባ ሥርዓት ያለፉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከማህበረሰቡ ጋር መልሶ በመቀላቀል የኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ እስከ አሁን በኮሚሽኑ የተከናወኑ የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች እንዲሁም ከልማት አጋሮች ጋር በሚሰራባቸው የአጋርነትና ትብብር መስኮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ተጠሪ መሐመድ አብዲከር ተቋሙ ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ስራዎች ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ዘጠኝ አባላትን ከያዘው የአውሮፓ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ሁለቱ ተቋማት የኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ጉዞ እንዲሳካና ሁለንተናዊ ሰላም እንዲሰፍን በሁሉም መስኮች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።