በድሬደዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየታየባቸው ነው

መጋቢት 22/2015 (ዋልታ) በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እየታየባቸው ስለመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሀር ድሬዳዋ በሀገር ምጣኔ ሀብት ላይ የሚኖራትን አስተዋፅኦ ከፍ የማድረግ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን የከተማዋ የልማት እንቅስቃሴን ጉብኝት በማድረግ ላይ ለሚገኘው የመገናኛ ብዙሃን ቡድን ገልፀዋል።

የድሬዳዋ ከተማን ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ የማስቀጠል ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ከንቲባ ከድር ፤ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ነው የገለፁት።

በተለይም በከተማዋ የሚገኘው የነፃ ንግድ ቀጣና የከተማዋን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳነቃቃው አብራርተዋል።

ከዚህ ባሻገር የደረቅ ወደብ አግልግሎት በከተማዋ በተገቢው መንገድ እየተሰጠ እንደሆነ ገልፀዋል።

ድሬዳዋን ምቹና ተመራጭ ሆና እንድትቀጥል የመሰረተ ልማት ስራዎች እንድ መንገድ ላይ መብራት፣ የጤና ተደራሽነት እንዲሁም የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግሮችን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በከተማዋ ከዚህ ቀደም የሚታዩ የሰላምና ፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት ለማስወገድ ከወጣቾችና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በጋራ በመስራት ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ነው ከንቲባ ከድር የገለፁት።

ከዚህም ባሻገር ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በስፓርት ዘርፍ መሰራቱ ተመላክቷል።

ሰለሞን በየነ (ከድሬዳዋ)