ርዕሰ መስተዳድሩ ዶና ፍራንሲስ ዘር እና እምነት ሳይገድባቸው ለሰብዓዊነት የኖሩ ባለውለታ ስለመሆናቸው ገለጹ

መጋቢት 23/2015 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ዶና ፍራንሲስ ለብዙዎች መለወጥ የጣሩ፣ ዘር እና እምነት ሳይገድባቸው ለሰብዓዊነት የኖሩ ባለውለታ ስለመሆናቸው ገለጹ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ ትውልድ እና እድገታቸው አሜሪካ ሆኖ አሁን ላይ ከሀዋሳ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚትገኘው ዶሬ ባፈኖ መንደር የሚኖሩትን ዶና ፍራንሲስን ጎብኝተዋል፡፡

አሜሪካዊቷ ዶና በ2000 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን በመንከባከብ እና በሌሎች በጎ ተግባር ስራዎች ተሰማርተው እንደቆዩና አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር እንደተዳረጉ ተመላክቷል፡፡

ላለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ የኖሩት ሲስተር ዶና ከጉራጌ ዞን ጀምሮ በኢትዮጵያ ያከናወኑትን ስራ ለርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል፡፡

በዚህም በበጎ ፈቃደኝነት ድንበር ሳይገድባቸው ብሄር እና ቀለም ሳይለዩ ላከናወኑት መልካም ስራ በርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡

በጤና እክል እንዲሁም በእርዳታ አቅራቢዎች አለመኖር በጎ ስራቸውን ለመቀጠል መቸገራቸውን ያስረዱት ሲሰትር ዶና ኢትዮጵያን ለቀው መሄድ እንደማይፈልጉም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስትም በጎ ፈቃደኛዋን ለማገዝ ቃል ገብቷል፡፡

አንተነህ ደጀኔ (ከሀዋሳ)