ድርቅ ከብቶቻችንን ቢነጥቀንም የተሻለን ነገ በማሰብ በጉልበት እያረስን ነው – የቦረና ዞን ነዋሪዎች

መጋቢት 29/2015 (ዋልታ) ድርቅ ከብቶቻችንን ቢነጥቀንም የተሻለን ነገ በማሰብ በጉልበት እያረስን ነው ሲሉ የቦረና ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ድርቁ በእጅጉ እንደጎዳቸው ገልጸው የዘር እጥረት በመኖሩ ከዚህ ቀደም አንድ ኪሎ ግራም በቆሎ በ30 ብር ይገዙ እንደነበረና አሁን ላይ በ150 ብር እየገዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ችግሩ እንዲቀረፍ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቦረና ዞን ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጀልዴሳ ዱባ በዞኑ በድርቅ ምክንያት ከ68 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸው በአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅት ዝናብ ባለመዝነቡ በተከሰተው ድርቅ በርካታ እንስሳት መሞታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የህብረተቡን ችግር ለመቅረፍ 43 የሚሆኑ ትራክተሮች ወደ ስራ ቢገቡም ፍላጎቱና አቅርቦቱ ባለመመጣጠኑ አብዛኛው አርብቶ አደር በጉልበት ለማረስ ተገዷል ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩ በመንግስት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የተራድዖ ድርጅቶችም የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ዙፋን አምባቸው (ከቦረና)