የአማራ ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን የተወሰነ ውሳኔ የለም – ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ሚያዝያ 1/2015 (ዋልታ) የአማራ ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን የተወሰነ ውሳኔ የለም ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ በሀገር ደረጃ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ለማደራጀት መወሰኑን ተናግረው ወደ ትግበራም መገባቱን ገልጸዋል።

ውሳኔው በፌዴራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት ስምምነት የተወሰነ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነም ተናግረዋል።

በአማራ ክልልም ውሳኔውን ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአፈጻጸም ላይ በታየ ክፍተት እና በተነዛው ፕሮፖጋንዳ ችግሮች መከሰታቸውን መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ችግር እንኳን ቢኖር ተወያይቶ መፍታት ይቻላል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ አብዛኛው የልዩ ኃይል አባል ውይይቱን አጠናቆ ውሳኔውን  በካምፕ ሆኖ እየተጠባበቀ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ጀግና ልዩ ኃይል ነው፣ መስዋእትነት የከፈለ ልዩ ኃይል ነው፣ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ሆኖ የሀገርን ሕልውና እና ሉዓላዊነት የጠበቀና ያስከበረ ነው፣ ይህ ልዩ ኃይል ትጥቅ የሚፈታና የሚበተን አይደለም፣ በላቀ አደረጃጃት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡

ልዩ ኃይሉ ዓላማውን ተገንዝቦ ለበለጠ ተልእኮ እንዲዘጋጅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ በሁኔታው ቅሬታ ውስጥ መግባቱን የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ ቅሬታው የመነጨው በተሟላ መንገድ ለሕዝቡ መረጃ ባለመድረሱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዓላማው የሀገር አንድነትን የሚያጸና፣ አብሮነትን የሚያስቀጥል እና የጸጥታ መዋቅሩ በክልልም ሆነ በፌዴራል የተናበበና ሕግን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ማድረግ ነውም ብለዋል፡፡

አደረጃጀቱ የሚደገፍ፣ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የሀገርን አንድነት የሚያረጋግጥ መሆኑንና የአማራን ክልል በተለየ መንገድ የሚጎዳ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን የታለመ ዓላማ እንደሌለ  አስገንዝበዋል፡፡

በተፈጠረው የመረጃ ክፍተት በአንዳንድ ከተሞች የሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴ፣ የአድማ ጥሪ እና የሰዎች እና የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴን የመገደብ አዝማሚያዎች እያታዩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አላስፈላጊ አካሄዶች አውዳሚ እና አክሳሪ እንጂ አትራፊ አለመሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል በጦርነት የከረመ ክልል ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በጦርነቱ ምክንያት ሕዝቡ ተጎሳቁሏል፣ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳው ኅብረተሰብ እና መሠረተ ልማት ገና ማገገም አልቻለም ብለዋል፡፡ ከአንደኛው ችግር ሳናገግም ወደ ሌላ ችግር መሸጋገር ሕዝቡን መጉዳት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመወያየት አላስፈላጊ ጉዳዮችን ማስቆም እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ ሁሉም አውዳሚ የሆነውን ጉዳይ መከላከል እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ግጭት እንዳይፈጠር ወጣቶች እና የሃይማኖት አባቶች የሚመሰገን ሥራ እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን በውል በማጤን፣ በመመካከር እና ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ በማሰብ ማስከን ይገባልም ብለዋል፡፡

የአማራ ልዩ ኃይል በተለየ መንገድ የሚጎዳ ውሳኔ አልተወሰነም፣ ወጥና ሀገራዊ ውሳኔ ነው የተደረገው፣ በሁሉም ክልል የሚፈጸም ነው፣ ውሳኔው ለሀገር ግንባታ ታላቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው እናምናለንም ብለዋል፡፡

ከወቅታዊ ጉዳይ አንጻር የሚነሳው ጥያቄ ትክክል ቢሆንም አፈጻጸሙ ለሀገር የሚጠቅም መሆኑን መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ከካምፕ የወጡ የልዩ ኃይል አባላት እንዲመለሱ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

በረጅም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪኩ እና በስርዓት አክባሪነቱ የሚታወቀው የአማራ ሕዝብ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማየት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ችግሩ ዳር ወጥቶ ግጭት እንዳይከሰት እያደረጉ ላሉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የልዩ ኃይል አባላት ትጥቅ አትፈቱም፣ የምትበተኑበት ነገር የለም፣ ወደ ላቀ ተልእኮ ነው የምትሽጋገሩት፣ ይሄን አውቃችሁ ለሀገራችሁ እና ለክልላችሁ ስታደርጉት የነበረውን አስተዋጽዖ በተሟላ መንገድ ለማስቀጠል እንድትችሉና እንድትዘጋጁ አደራ እላለሁም ብለዋል፡፡

በመደማመጥ ችግሮቻችን እንፈታለን፣ የአማራን ጥያቄዎች እናስመልሳለንም ነው ያሉት፡፡