አባይ አፍሪካዊ ወንዝ በመሆኑ አጀንዳው አህጉራዊ መሆን አለበት – የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር

ሚያዝያ 3/2015 (ዋልታ) አባይ አፍሪካዊ ወንዝ በመሆኑ አጀንዳው አህጉራዊ መሆን እንዳለበት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ጋር ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ስለሚገኝበት ሁኔታ አምባሳደር ምስጋኑ ገለፃ አድርገዋል ።

ሚኒስትር ዲኤታው የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት የኢትዮጵያን አቋም ለሊቀመንበሩ ያስረዱ ሲሆን የሦስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስራ መከናወኑ መቀጠል እንዳለበት ኢትዮጵያ የፀና አቋም እንዳላት ገልፀዋል።

ግብፅ የአባይን ውሃና ግድቡን የፖለቲካ መልክ ለማሰጠት እየሄደች ያለችበት መንገድ የትኛውንም አካል የሚጠቅም አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ይህን እንቅስቃሴ በማቆም መሬት ላይ ያለውን እውነት መነሻ ያደረገ ወይይትና ድርድር እንዲቀጥል ህብረቱ በጎ ሚናውን ይወጣል ሲሉ ያላቸውን እምነት አንስተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ የአፍሪካ ህብረት በአሁን ሰዓት እያከናወነ ያለውን ተቋማዊ ሪፎርም ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ የገለፁ ሲሆን ለህብረቱ ስኬታማ ጉዞ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

በአዲሱ የሪፎርም ማሻሻያ ሲደረግ በተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን መብትና ጥቅምን ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበትም ጠይቀዋል።

የህብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት በበኩላቸው አባይ አፍሪካዊ ወንዝ በመሆኑ አጀንዳው አህጉራዊ መሆን እንዳለበት ህብረቱ እንደሚያምን ገልጸዋል።

ድርድሩም በአፍሪካ ማዕቀፍ እልባት እንዲያገኝ ህብረቱ የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግዋል።

ህብረቱ በሚያከናውነው ተቋማዊ ሪፎርምም የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ባከበረ መልኩ እንደሆነ ማረጋገጣቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡