የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ወደ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ መሸጋገሯን ማሳያ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አምባሳደር መለስ ዓለም

ሚያዝያ 10/2015 (ዋልታ) የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ተከታታይ ጉብኝት ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ መሸጋገሯን አመላካች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር ፒተር ሲያርቶ ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በሀገራቱ ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነቶችን ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ከሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር ፒተር ሲያርቶ ጋር ስኬታማ ውይይት መካሄዱን እና የሁለቱ ሀገራትን ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ፣ በአካባቢያዊ እና በባለብዙ ወገን የትብብር መድረኮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው የጸጥታ ችግር ለመፍታት የተጀመረውን የሰላም ስምምነት ትግበራ በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ እና ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ከሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር በበኩላቸው በኢኮኖሚ እና በሲቪል አቪየሽን መስክ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት እንዲደረግ ለቀረቡት ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃደኝነቱን መግለጹንም አምባሳደር መለስ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ በኩል የተለዬ ትኩረት በመስጠት እሰራች ያለችባቸው አቅጣጫዎች ወዳጆችን የማብዛት፣ ግብዛቤ መፍጠር እና  ችግሮችን የማለዘብ ስትራቴጂን እየተገበረች መሆኗን ኢዜአ በዘገባው አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት እና በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተች ስለመሆኗ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ውይይት መደረጉም ተገልጿል፡፡