የ1444ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓል በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት ተከበረ

ሚያዝያ 13/2015(ዋልታ) የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያለፈውን አንድ ወር በፆም፣ በፀሎት እንዲሁም በመረዳዳት አሳልፎ ዛሬ 1444ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓል በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት አከበረ።

ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለመላው ዓለም ህብረተሰብ በዓሉ የሰላም የደስታና የፍቅር ሲሆን፤ ኢድ አልፈጥር ሙስሊሙ ሕብረተሰብ የተቸገሩ ወገኖቻችን በማሰብና በመርዳት በመተዛዘን የሚከበር በዓል ነው።

ኢድ – አልፈጥር ትርጉሙ ራሱ የፆም ማጠናቀቂያ ክብረ – በአል እንደማለት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ሁሉም አማኞች በጧት ተነስተው ልዩ የሶላት ስግደት ወደሚደረግበት ስታዲየም ቦታ በመትመም በድምቀት አክብረውታል።

የእምነቱ ተከታዮች በቡድን እየሆኑ ተክቢራ በማድረግ (የበአሉ የውዳሴ ዜማዎች) የተከበረ ሲሆን፤ የጋራ የሶላት ስግደትም ተከናውኗል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖች በመርዳት ፣የታረዙትን በመልበስ የተረቡትን በመብለት የመተዛዘንና የመደጋገፍ የጉርብትና ፍቅር ዘመድ ከዘመድ ጓደኛ ከጓደኛ የሚዘያየርበት በረመዳን ወቅት የነበረው በጎ ተግባርና ስነ- ምግባር መጠናከርና መቀጠል እንዳለበት መልዕክት ተላልፏል።