የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ሚያዝያ 13/2015(ዋልታ) የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1 ሺህ 444ኛው ዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙሰጠፌ መሀመድ በበኩላቸው፣ ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥርን በዓል ሲያከብር በመተዛዘን፣በመተሳሰብ፣በመተጋገዝና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ወቅት የታየው የመደጋገፍንና መረዳዳት እሴት በማጠናከር እንዲሁም ሰላምንና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር ያስፈልጋልም ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ÷ዒድ አል ፈጥር ዕዝነት፣ ርህራሄ፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍና አንድነት የሚጠናከርበት ነው ብለዋል።

የረመዳን ፆም ሃይማኖታዊ ሥነ-ምግባርን ጠብቆ የሚፆም ታላቅ ወር በመሆኑ የዒድ-አልፈጥር በዓልን ስናከብርም ሃይማኖታዊ ሕግጋቱ በሚፈቅደው መሰረት ለአካባቢያችን ሰላም በጋራ ዘብ በመቆም ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ዑንዴ፣ እንደ ሀገር የተጀመሩ የሰላም፣ የልማት፣ የእድገት እና ብልፅግና ጉዞዎችም ግባቸውን እንዲመቱና ኢትዮጵያችን ወደተሻለ የከፍታ ማማ መሸጋገር እንድትችል በመደማመጥ፣ በመግባባትና አርቆ በማሰብ ሁላችንም የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት አሻራ ልናሳርፍ ግድ ይለናል ብለዋል።

አንድ ሙእሚን አላህን በመታዘዝ፣ እሱን በመዘከርና በማመስገን ያሳለፈው ቀን በሙሉ ኢዱ ነውና በህይወት ዘመናችን ሁሉ ኢባዳዎቻችንን ለአላህ ጥርት በማድረግ ለሀገራችን የሚጠበቅብንን እየፈፀምን የምናሳልፋቸው ቀናት በሙሉ ኢዳችን የደስታ ቀናቶቻችን መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ፣መረዳዳት እና መደጋገፍ ጎልቶ በሚታይበት የረመዳን የጾም ወቅት የታየው መልካም እሴት በቀሪ ጊዜያትም ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

የኢድ አል ፊጥር በዓል የእዝነትና የርህራሄ የመተሳሰብ፣ ያለው ለሌው በማካፈል በአብሮነት የሚያሳልፈው እና ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር በመሆኑ መላው ህዝበ ሙስሊም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዓሉን በመደጋገፍ እና በመረዳዳት ሊያሳልፍ ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው መልህዝበ ሙስሊሙ ታላቁንና የተከበረውን የረመዳን ወር በጾም፣ በዱዓ፣ በሶደቃ፣ በመተጋገዝ፣ በመረዳዳትና አርአያነት ባላቸው ሌሎች ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ማሳለፉን አስታውሰዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህን በረመዳን ወር ያዳበራቸውን መልካም እሴቶች ከረመዳን ውጪ ባሉ ጊዜያትም ተጠንክረው መቀጠል አለባቸው:: የእስልምና እምነት ተከታዮችም እርስ በእርስና ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድም እህቶቹ ጋር ለዘመናት የገነባውን ፍፁም መልካም መስተጋብር የበለጠ በማጠናከር በሀገሪቱ ልማትና ሰላም ግንባታ ላይ ሚናውን በትጋት ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብርም ያለንን በማካፋል አቅመ ደካሞችን በመጠየቅና የተለመደውን እርስ በርስ የመረዳዳት ልምድ በማጎልበት መሆን እንዳለበት አስታዉሰዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ለመላው እስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣የጤና፣የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡