በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጥቅምና ደህንነት የሚያስከብር ሕጋዊ ሥርዓት መዘርጋቱ ተገለጸ

ሙፈሪሃት ካሚል

ሚያዝያ 14/2015 (ዋልታ) በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጥቅም፣ መብትና ደህንነት ማስከበር የሚያስችል ሕጋዊ ሥርዓት መዘርጋቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከውጭ አገራት የሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በእርሳቸው የተመራ ልዑክ በቤይሩት፣ ሊባኖስና ሳዑዲ አረቢያ ተዘዋውሮ ዜጎች የተሻለ ደመወዝ እንዲከፈላቸው፣ መብትና ደህንነታቸው እንዲከበር ለማድረግ ከአገራቱ መንግሥታት ጋር ስምምነት መደረጉን አስታውቀዋል።

የተደረሰው ስምምነት ዜጎች ወደነዚህ አገራት በሕጋዊ መንገድ ገብተው መሥራት እንዲችሉ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሯ የአገሪቱ መንግሥት ከአሠሪዎች አያያዝ፣ ከሠራተኞች ደመወዝ ክፍያ፣ ከእረፍት ጊዜ አሰጣጥ፣ ከመብት እና ደህንነት አጠባበቅ አንጻር ክትትል እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

የተዘረጋውን ሥርዓት ተከትለው በሕጋዊ መንገድ ወደ ሊባኖስ አገር ለሚሄዱ ሠራተኞች ትርጉም ያለው ደመወዝ እንዲከፈላቸውና መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ያስችላልም ብለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ በነበራቸው ቆይታ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍላጎት መኖሩን ማረጋገጣቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ሠራተኞች ትርጉም ያለው የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ፣ መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ መነጋገራቸውንም ጠቁመዋል።

ስምምነቱን ከዚህ በፊት ሠራተኞች በሕገወጥ መንገድ ሲኖሩ ሕጋዊ ከለላ እንዳይኖራቸው ይደረጉ የነበሩትን ችግሮች ከመቅረፉም ባለፈ ሕገወጥ የሰዎች ፍልሰትን እንደሚያስቀር አብራርተዋል።

አንድ ሰው ለሥራ በሚሄድበት አገር ሁለት ዓመት የኮንትራት ውል የሚፈራረሙ ሲሆን ካልተመቻቸው በሕጋዊ መንገድ የመቀየር መብት እንዳላቸው መግለፃቸውን የኢፕድ ዘገባ አመላክቷል።